![](wp-content/uploads/2025/01/Garowe-1140x570-1.jpg)
አዲስ አበባ፣ ጥር 21/2017 ዓ.ም፡- በበርካታ ሀገራት በአሸባሪነት ከተፈረጀው ከአይኤስ (ISIS) ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል ከፊል ራስ ገዝ በሆነችው የሶማሊያዋ ግዛት ፑንትላንድ የሚኖሩ ሶስት ኢትዮጵያውያን በሁለት ቀናት መገደላቸው ተገለጸ፤ በርካቶች ደግሞ ለእስር ተዳርገዋል።
በፑንትላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለአዲስ ስታንዳርድ እንዳስታወቁት የፑንትላንድ ዋና ከተማ የሆነችው ጋሬዌን ጨምሮ በግዛቲቱ በሚገኙ ቦሳሶ እና ካልካዋ በተባሉ ከተሞች ኑሯቸውን ያደረጉ እና በስደት ተጠልለው በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ “ጥቃት፣ የዘፈቀደ እስር፣ ግርፋት እና ዝረፊ” እንደተፈጸመባቸው አስታውቀዋል።
በቦታው የሚገኙ የአይን እማኞች እንዳስታወቁት ከሶስተ ቀናት በፊት ጥር 18 ቀን 2017 የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች አንድ ኢትዮጵያዊ መግደላቸውን ተከትሎ ግጭት ተቀስቅሶ እንደነበር ጠቁመዋል፤ በነገታው ደግሞ ሁለት ኢትዮጵያውያን በቦሳሶ ከተማ “በህዝቡ ተደብድበው” ተገድለዋል ብለዋል።
ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የፑንትላንድ ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት ግድያው ኢትዮጵያውያን “ከአሸባሪው አይኤስ (ISIS) ጋር ግንኙነት አላቸው” የሚል ውንጀላ ጋር የተያያዘ ነው።
በበርካታ ሀገራት በአሸባሪነት የተፈረጀው አይኤስ(ISIS) በፑንትላንድ ውስጥ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ሲሆን ከአልሸባብ እና ከየመን አማጽያን ሁቲ ታጣቂዎች ጋር ግንኙነት እንዳለው ይነገራል።
ይሁን እንጂ አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገራቸው እና ኢትዮጵያውያኑ ለምን የጥቃት ሰለባ ሆኑ ሲል የጠየቃቸው የፑንትላንዱ ነዋሪ “ከቡድኑ ጋር ግንኙነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ሊኖሩ እንደሚችሉ” ጠቁመው ነገር ግን “ጥቂት ግለሰቦች ከዚህ ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው ተብሎ ሁሉንም ኢትዮጵያውያንን መቅጣት ተገቢ አይደለም” ብለዋል።
የፑንትላንድ አስተዳደር የጸጥታ ሃይሎች “በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ማሰራቸውን” ያነጋገርናቸው ነዋሪው አክለው ገልጸዋል። “በዋና ከተማዋ ጋርዌ ውስጥ ብቻ ከ500 በላይ ኢትዮጵያውያን በመንግስት ባለስልጣናት ታስረዋል” ሲሉም አስታውቀዋል፤ ለእስር የተዳረጉት ከታጣቂ ቡድኑ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ንጹሃን ናቸው ብለዋል።
አዲስ ስታንዳርድን ያነጋገራቸው ሌላኛው በፑንት ላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ በበኩላቸው እየተወሰደ ያለው እርምጃ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነቱን ከፈጸመች በኋላ እየጨመረ የመጣው በኢትዮጵያውያን ላይ ያለው ጥላቻ ጋር የተያያዘ ነው ሲል ገልጿል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሟን ተከትሎ ተመሳሳይ ጥቃት ተፈጽሞ እንደነበር ያስታወሰው ነዋሪው “ይህ በጥላቻ ካልተነሳሳ በስተቀር በሌላ ምክንያት የዚህ አይነት ጥቃት ሊፈጸም አይችልም” ሲል አስታውቋል።
ነዋሪው በተጨማሪም ፖሊስ እና ሚሊሻዎችን ጨምሮ የፑንትላንድ የጸጥታ ሃይሎች በኢትዮጵያውያን ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ እንደነበር ተናግሯል።
የፑንትላንድ ነዋሪዎች “ኢትዮጵያውያኑ አገራቸውን ለቀው እንዲወጡ እና ንብረታቸውን ጥለው እንዲሄዱ በማስፈራራት ላይ ናቸው” ሲል ስሞታ አቅርቧል።
“ይህ አሁን የሚሉት ጉዳይ ብቻ አይደለም፣ አንዳንድ ሶማሊያውያን በኢትዮጵያውያን ላይ ያላቸው ጥልቅ ቅሬታ ማሳያ ነው” ሲል በመግለጽ ግድያ፣ ጥቃት፣ ዛቻ እና ዘረፋ እየቀጠለ የሚገኝ ተግባር መሆኑን አመላክቷል። አስ