![](wp-content/uploads/2025/01/1_mp7Ok9_odsJ21MedBdqXUw.webp)
አዲስ አበባ፣ ጥር 22/2017 ዓ.ም፡- የፑንትላንድ ፖሊስ በክልሉ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ተገድለዋል መባሉን “ሀሰት” ሲል ውድቅ አደረገ። ይሁን እንጂ ስደተኞች ላይ ድንጋይ የመወርወርና መሰል “እነስተኛ ክስተቶች” እንደነበሩ በመግለጽ ጥፋተኞች “በቁጥጥር ስር መዋላቸውን” አስታውቋል።
የፑንትላንድ ፖሊስ ጥር 21 ቀን 2017 ዓ.ም በማኅበራዊ ሚዲያ አጭር መግለጫ፣ “በፑንትላንድ የተገደሉ ኢትዮጵያያውያን የሉም” ሲል “ዘገባዎቹ ትክክል እንዳልሆኑ” ገልጿል።
አክሎም የአከባቢው ባለሥልጣናት “መሰል ዓይነት ድርጊቶች እንዳይፈፀሙ ማስጠንቀቂያ” የሰጡ ሲሆን “ሁሉንም ነዋሪዎች ለመጠበቅ” ቁርጠኛ መሆናቸውንም አመልክቷል።
ፖሊስ ማስተባበያውን የሰጠው ከአይኤስ ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል በፑንትላንድ ሶስት ኢትዮጵያውያን በሁለት ቀናት መገደላቸውንና በርካታ ኢትዮጵያውያን መታሰራቸውን ነዋሪዎች ዋቢ አድርጎ ለአዲስ ስታንዳርድ መዘገቡን ተከትሎ ነው።
በቦታው የሚገኙ የአይን እማኞች እንዳስታወቁት ከሶስተ ቀናት በፊት ጥር 18 ቀን 2017 የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች አንድ ኢትዮጵያዊ መግደላቸውን ተከትሎ ግጭት ተቀስቅሶ እንደነበር ጠቁመዋል፤ በነገታው ደግሞ ሁለት ኢትዮጵያውያን በቦሳሶ ከተማ “በህዝቡ ተደብድበው” ተገድለዋል ብለዋል።
በክልሉ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችም በተለይ ዋና ከተማዋን ጋሮዌ ጨምሮ ቦሳሶ እና ካልካው በተሰኙ ከተሞች ውስጥ የዘፈቀደ እስር፣ ድብደባ እና ዘረፋ ኢላማ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የፑንትላንድ አስተዳደር የጸጥታ ሃይሎች “በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ማሰራቸውን” ነዋሪዎች አክለው ገልጸዋል። “በዋና ከተማዋ ጋርዌ ውስጥ ብቻ ከ500 በላይ ኢትዮጵያውያን በመንግስት ባለስልጣናት ታስረዋል” ሲሉም አስታውቀዋል፤ ለእስር የተዳረጉት ከአይ ኤስ ቡድን ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ንጹሃን ናቸው ብለዋል።
ይህ በፑንትላንድ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ዒላማ ካደረጉ ተከታታይ ክስተቶች ውስጥ አንዱ እና የቅርብ ጊዜው ነው።
በቅርቡ በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም የፑንትላንድ ባለስልጣናት “ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ቁጥራቸው እየጨመረ መሄዱን እና ይህም በአካባቢያዊ የስራ እድሎች ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን” በመጥቀስ ህጋዊ ሰነድ ሳይኖራቸው “በህገ-ወጥ መንገድ” በዋና ከተማዋ ጋሮዌ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በአስቸኳይ እንዲወጡ የሚያስገድድ ትዕዛዝ ማውጣቱ ይታወሳል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ፤ ሶማሊያ “ሉዓላዊነቴን እና የግዛት አንድነቴን ይጥሳል” ስትል የተቃወመችውን የባሕር በር ስምምነትን ከሶማሌላንድ ጋር መፈራረሟን ተከትሎ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የሚደርስባቸው ዛቻና ጥቃት እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።አስ