![](wp-content/uploads/2025/01/photo_2022-07-03_23-59-58-1200x645.jpg)
አዲስ አበባ፣ 20/ 2017 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከ75 በላይ አባላቱ “ፍትሕ ተነፍገው” በእስር ላይ እንደሚገኙ በመግለጽ እየደረሰባቸው ያለው “እስር፣ ግፍና ወከባ” በአስቸኳይ እንዲቆምና ነፃ እንዲሆኑ ጠየቀ፡፡
ፓርቲው ዛሬ ጥር 20/2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የገዢው ፓርቲ ኃላፊዎችና የመንግሥት አካላት፤ ከፊታችን ይደረጋል ተብሎ በሚታሰበው ሀገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ በሚመስል መልኩ እና “በተናበበ ሁኔታ” በሰው ኃይል እና ፋይናንስ መደራጀትን ለማዳከም በማሰብ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ አባሎቻችንን በማሠር እና ማወከብ ላይ ተጠምደው ይገኛሉ ሲል ከሷል።
በዚህም ጠንካራ ድርጅታዊ መዋቅር መፍጠር እንዲሁም በሕገመንግስቱም በግልጽ የተቀመጠውን የመደራጀት መብትን በሚጥስ መልኩ ከ76 በላይ አባላቱ ላይ “ግፍ ወከባና እስር” እየተፈፀመ መሆኑን ገልጿል።
ኢዜማ በመግለጫው በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጎንደር ከተማ ተፈራ ሙጬ የተባሉ አባላችን ከጥር 7 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር ላይ ይገኛሉ ብሏል። በደቡብ ወሎ ዞን የአምባሰል ምርጫ ክልል ሰብሳቢ የሆኑት ልዑልሰገድ አብረሃ ከጥቅምት 7 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር ላይ እንደሚገኙና ፍ/ቤት አለመቅረባቸውንም አክሎ ገልጿል።
በጋሞ ዞን አርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ዘይሴ ምርጫ ክልል ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት እስር ላይ የቆዩ 77 አባላቶች ከእስር ቢፈቱም አሁንም እስር እና እንግልቱ ቀጥሎ መፍትሔ ባለመገኘቱ ምክንያት ከ50 በላይ አባሎቻችችን ፍትሕ እና ፍርድ ሳያገኙ በእስር ላይ ይገኛሉ ብሏል፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አሪ ዞን ባኮ ጋዘር 1 ምርጫ ክልል እና በጋርዱላ ዞን 23 አባላት የገዢው የብልጽግና ፓርቲ እና የመንግሥት አካላት በዞኑ ከብልጽግና ፓርቲ ውጪ የሚንቀሳቀስ ሊኖር አይችልም በሚል በእስር ላይ ይገኛሉ ሲል ገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም በሀረሪ ክልል ሀረር ከተማ የኢዜማ አስተባባሪ እና የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ም/ሰብሳቢ ማሕሌት ዘውዱ ከጥር 8 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በሀረሪ ፖሊስ ኮሚሽን “ያለበቂ ምክንያት” የዋስ መብት እንኳ ተከልክላ በእስር ላይ እንደሚገኙ ኢዜማ አስታውቋል።
በአባላቶቹ ላይ የተፈጸመው ድርጊት እንዳሳዘነው የገለጸው ድርጅቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው እስር ወከባና ግፍ የሰላማዊ ፖለቲካ ትግል ላይ አደጋ መደቀን እና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ቁርጠኛ አለመሆን አድረገን እንወስደዋለን ብሏል።
አክሎም ሀገራችንን ወደኋላ እየጎተቱ የተለመደ አዙሪት ውስጥ እንዳይከተን ያሰጋናል ሲል ገልጿል፡፡ በመሆኑም አባሎቹ እየደረሰባቸው ካለው ግፍ ወከባና እስር ነፃ እንዲሆኑ በአፅንኦት ጠይቋል፡፡
በሀገራችንም በገዢው ፓርቲ እና ተፎካካሪዎች መካከል “እንደ ባሕል የተገነባው ከእኔ ሐሣብ ውጪ ሌላው በፍፁም ትክክል አይደለም” የሚል እሳቤ ዘመናዊ የፖለቲካ ፓርቲ ሥርዓትን ከጀመርን አንስቶ “የተጫነን ቀንበር” ሆኖ እናገኘዋለን ሲልም ገልጿል።
ኢዜማ በዚህም ምክንያት ገዢው ሌሎች ተፎካካሪዎችን “በማሠር፣ በመግደል፣ እንዲሠደዱ በማድረግ እና ሌሎች ማዋከብያ” መንገዶችን በመጠቀም አንድ አውራ ገዢ ፓርቲ እንደ ልቡ የሚሆንበት ሥርዓት እንደ ባሕል ተጣብቆን ይገኛል ብሏል በመግለጫው። አስ